Back

ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለመጠቀም የሚያስችላትን ስምምነት ከሩስያ ጋር ተፈራረመች

OBN ሚያዚያ 08፣2011  ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን በህክምና፣ በግብርናና በኢንደስትሪ ዘርፍ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችላትን የትግበራ ስምምነት ከሩስያ ጋር ተፈራረመች።

በተለይ በዓለም እያደገ የመጣውን የህምና ዘርፍ በኢትዮጵያ ለማዘመንና የቀዶ ጥገና ህክምናን የተቀላጠፈ ለማድረግ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚሰራ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂ ጌታሁን መኩሪያ ተናግረዋል፡፡

ስምምነቱ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን ለመገንባት በዝናብ ላይ ጥገኛ ከሆነው የሃይል ማመንጫ በተጨማሪ ድብልቅ ኢነርጂ አማራጮችን ለመጠቀም የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በሩስያ በተካሄደው 11ኛው "አቶም ኤክስፖ" ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂ ጌታሁን መኩሪያና የሩስያ ስቴት አቶሚክ ኢነርጂ ኮርፖሬሽን ዳይሬክተር ጀነራል አሌክሲ ሌካቼቭ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል የትግበራ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የትግበራ ፍኖተ ካርታ ስምምነቱ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን በግብርና፣ የህክምናውን ዘረፍ ለማዘመን፣ ለማምረቻው ዘርፍ ግብዓትና ለመሳሰሉት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

11ኛው የአቶም ኤክስፖ በሩስያ ሲቺ ከተማ መካሄዱን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡