Back

በኦሮሚያ ክልል ተሽከርካሪዎች ላይ የተሞከረው የፍጥነት መቆጣጠሪያ አደጋን መቀነስ ማስቻሉ ተገለፀ

 

 
 

 [ኦሪድቴ 07 01 2009] በኦሮሚያ ክልል የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ የተሞከረው የፍጥነት መቆጣጠሪያ ከልክ በላይ በማሽከርከር የሚፈጠር አደጋን ለመቀነስ አስችሏል ተባለ።

ባለፈው አመት በኦሮሚያ ክልል ከተከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች ውስጥ ሰማንያ በመቶው በፍጥነት በማሽከርከር የተከሰቱ መሆናቸውን ከክልሉ ትራንስፖርት ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

ይህን ችግር ለመቀነስ ባለስልጣኑ በተመረጡ ተሽከርካሪዎች ላይ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ መግጠምን በመፍትሄነት ሲተገብር ቆይቷል።

ከ2008 ሚያዚያ ወር ጀምሮ ሲተገበር በቆየው ፕሮጀክት፥ በጥቂት የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሳሪያው ተገጥሞ ታይቷል።

ባለስልጣኑ ባደረገው ግምገማም የሙከራ መሳሪያው የተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎችን በፍጥነት ምክንያት ከሚከሰት አደጋ መታደግ መቻሉን ገልጿል።

የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሆኑ አሽከርካሪና ባለቤቶችም የአደጋ ተጋላጭነቱ እንደቀነሰ ጠቅሰው፥ ለሰው ህይዎትና ንብረት ደህንነት ዋስትና መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙስጠፋ ከድር፥ በተደረገው ሙከራ የተገኘው ውጤት ዜጎችን በትራፊክ አደጋ ከሚከሰት ሞት እና የአካል ጉዳት እንዲሁም ንብረትን ከውድመት መታደግ ለመቻሉ ማሳያ ነው ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ የታየውን ውጤት ተከትሎ በያዝነው አመት በክልሉ በሚሰሩ አነስተኛ እና መካከለኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ መሳሪያው ይተከላልም ነው ያሉት።

በሂደት በሌሎች ተሸከርካሪዎች ላይ እንደሚተገበር ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በክልሉ የሚገኙ የመንግስት ተሽከርካሪዎች ላይም ተሽከርካሪዎቹ የሚገኙበትን ቦታ መጠቆም የሚያስችል መሳሪያ በያዝነው አመት እንደሚተገበር ተናግረዋል።

በመንግስት ተሽከርካሪዎች ላይ የሚተገበረው የቦታ መጠቆሚያ ቴክኖሎጂ በአንዳንድ አሽከርካሪዎች የሚስተዋለውን ነዳጅ ማጭበርበር ማስቀረት ያስችላልም ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።

ሴክተር መስሪያ ቤቶቹ ቴክኖሎጂውን እስከ 10 ሺህ ብር በሚደርስ ዋጋ የሚያስገጥሙ ሲሆን፥ ከሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በአሁኑ ወቅት የጋራ ስምምነት ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል።