Back

የ10 ቢሊየን ብር የወጣቶች ስራ ፈጠራ ተዘዋዋሪ ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅ ፀደቀ

 

 
 

[ኦሬቴ 30 05  2009] የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ10 ቢሊየን ብር የወጣቶች ስራ ፈጠራ ተዘዋዋሪ ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅን አፀደቀ።

ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ለተመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ ትግበራ የሚያግዝ፥ የተዘዋዋሪ ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅ ተዘጋጅቶ ምክክር ከተደረገበት በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።

ምክር ቤቱም አዋጁን ሲመለከተው ከቆየ በኋላ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው አጽድቆታል።

በአዋጁ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፈንዱን በፌደራል መንግስት ስም እንዲያስተዳድር ሃላፊነት ተሰጥቶታል።

በአዋጁ መሰረትም ብድሩ በአነስተኛ የገንዘብ ተቋማት አማካኝነት የሚፈጸም ይሆናል ነው የተባለው።

ተቋማቱ በማይገኙበት ሁኔታ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተቋማቱን ተክቶ እንዲሰራ ይደረጋል።

ከዚህ ባለፈም ፈንዱን በዝርዝር እየመረመረ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሪፖርት የሚያቀርብ ይሆናል።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርን ጨምሮ የክልልና የከተማ አስተዳደሮችም በየደረጃው ማስተግበር የሚያስችል ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።

ምክር ቤቱም ፈንዱ ትግበራ ላይ ውሎ ወጣቶቹ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ አቅጣጫ አስቀምጧል።

በአሁኑ ወቅትም ወጣቶችን የማሰልጠን፣ የመመልመል እና የፕሮጀክት ዝግጅት ስራው እየተጠናቀቀ ነው ተብሏል።

በተዘዋዋሪ ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጁ መሰረት ከ18 እስከ 34 አመት የእድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች በስራ እድል ፈጠራው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል።(ኤፍ ቢ ሲ)