Back

የሌስተር ሲቲው ባለቤት ሄሊኮፕተራቸው ተከስክሶ ህይወታቸው አለፈ፡፡

OBN ጥቅምት 192011  ከሁለት ዓመት በፊት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን ዋንጫ የበላው የእግር ኳስ ክለብ የሌስተር ሲቲው ባለቤት ቪቻይ ስሪቫዳናፕራባ የግል ሄሊኮፕተራቸው ከኪንግ ፓወር ስታዲየም ሲወጣ ተከስክሶ መሞታቸው ተዘግቧል።

የ60 ዓመቱ ታይላንዳዊ ቢሊዮነር ቪቻይ ስሪቫዳናፕራባን ጨምሮ የሄሊኮፕተሩ ሁለት ሰራተኞች፣ ዋና አብራሪና አንድ ሌላ ተሳፋሪ ሄሊኮፕተሯ ስትከሰከስ ወዲያው መሞታቸው ተረጋግጧል።

እንደ አይን እማኞች ገለጻ ከሆነ ሄሊኮፕተሯ ከኪንግ ፓወር ስታዲየም ተነስታ ገና አየር ላይ ብዙም ሳትቆይ ነው ከቁጥጥር ውጪ ሆና የተከሰከሰችው።

በሄሊኮፕተሯ ውስጥ ከነበሩት ተሳፋሪዎች መካከል አንዷ አብራሪ ኢዛቤላ ሌኮዊዝ የፖላንድ ዜግነት ያላት ሲሆን፤ በእንግሊዝ የሚገኘው የፖላንድ ኤምባሲ በተፈጠረው አደጋ ማዘኑን ገልጿል።

ሟቹ ቢሊዮነር በአውሮፓውያኑ 2010 ነበር የእንግሊዙን ሌስተር ሲቲ የእግር ኳስ ክለብን በ39 ሚሊዮን ፓውንድ የገዙት።

ክለቡን ከገዙት ከ5 ዓመታት በኋላ ደግሞ ማንም ሳይጠብቀው ሌስተር ሲቲ በ2016 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆን ችሏል።

ስዋፈር የተባለው ዋና አብራሪ ከሃያ ዓመታት በላይ የግል አውሮፕላንና ሄሊኮፕተር የማብረር ልምድ ያለው ሲሆን፤ ለተለያዩ የዜና አውታሮችም የቀጥታ ስርጭት ለመዘገብ የሚውሉ ሄሊኮፕተሮችን ለረጅም ዓመታት አብርሯል።

የሌስተር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ ባወጣው መግለጫ በተፈጠረው አደጋ ማዘኑን ገልፆ ህይወታቸው ላለፈ ሰዎች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቷል።

ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት የነበሩት ቪቻይ ደግሞ እጅግ ቸር የሆኑና በበጎ ምግባራቸው የሚታወቁ ሰው እንደነበሩም አክሏል።

ከማክሰኞ ጠዋት ጀምሮ ደግሞ በክለቡ ስታዲየም ኪንግ ፓወር የሃዘን መግለጫ መርሃግብር እንደሚኖር ተገልጿል።

ሌስተር ሲቲ በኢኤፍኤል ዋንጫ ማክሰኞ ምሽት ከሳውዝሃምፕተን ሊያደርገው የነበረው ጨዋታም ተራዝሟል።

የሌስተር ከተማ ፖሊስ ደግሞ ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን ገልጾ ከሄሊኮፕተሯ ውስጥ ከነበሩት ሰዎች ውጪ በማንም ላይ ጉዳት አለመድረሱን አስታውቋል።

ምንጭ፡- ቢቢሲ