Back

በ2018 የዓለም ምርጥ 10 ወንድ አትሌት እጩዎች ውስጥ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች መካተት አልቻሉም፡፡

[OBN  13- 02-2011] የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ዛሬ የ2018 የዓለም ምርጥ ወንድ አትሌት እጩዎችን ይፋ ያደረገ ሲሆን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዝርዝር ውስጥ አልተካተቱም። ትናንት ማህበሩ 10 የ2018 የዓለም ምርጥ ሴት አትሌቶች ይፋ ባደረገበት ወቅት ኢትዮጵያን አትሌቶች አለመኖራቸውን ጨምሮ በአጠቃላይ በሁለቱም ጾታዎች የዓለም ምርጥ አትሌት እጩዎች ዝርዝር ውስጥ መግባት አልቻሉም። በሁለቱም ጾታዎች የዓለም ምርጥ አትሌት እጩዎች ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አለመግባታቸው ባለፈው ዓመት የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ በሌሎች አገራት ተወዳዳሪዎች ብልጫ እንደተወሰደባቸውና በስፖርቱ ላይ መዳከም እንዳለ የሚያሳይ ነው። በዚሁ መሰረት ኬንያዊው የመካከለኛ ርቀት ሯጭ ቲሞቲ ቼሪዮት፣ አሜሪካዊው የአጭር ርቀት ሯጭ ክርስቲያን ኮልማን፣ ስዊድናዊው የምርኩዝ ዘላይ አርማንድ ዱፕላንቲስ፣ ኬንያዊው የዓለም የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት ኤሊዩድ ኪፕቾጌና ሌላኛው ኬንያዊ የአጭርና መካከለኛ ርቀት ሯጭ ኢማኑኤል ኮሪር በእጩ ዝርዝር ውስጥ መካተት ችለዋል። የስሉዝ ዘላዩ ሉቮ ማንዮንጋ ከደቡብ አፍሪካ፣ የአጭር ርቀት ሯጩ አብዱርሀማን ሳምባ ከኳታር፣ የአሎሎ ወርዋሪው ቶማስ ዋልሽ ከኒውዝላንድ፣ የእጭር ርቀት ሯጩ ኖህ ላይልስ እና የሄፕታትሎንና ዴክታትሎን (የሰባት እና አስር የአትሌቲክስ ስፖርት ዓይነቶች) ተወዳዳሪ ኬቨን ማየር ሌሎች 10 ምርጥ እጩ ውስጥ የገቡ አትሌቶች ናቸው። ኬንያ ሶስት እጩዎችን ስታስመርጥ በአጠቃላይ አራት አትሌቶች ከአፍሪካ አህጉር በእጩነት ተመርጠዋል። በዕጩነት ከሚቀርቡ 20 አትሌቶች የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማህበር ምክር ቤት፣ ቤተሰቦችና የአትሌቲክስ ደጋፊዎች በሚሰጡት ድምጽ ከሁለቱም ጾታዎች አምስት አትሌቶች በምርጥነት ይመረጣሉ። በድምጽ አሰጣጡ ኮታ መሰረት የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማህበር ምክር ቤት 50 በመቶ እንዲሁም የማህበሩ ቤተሰቦች ( IAAF Family's) እና የአትሌቲክስ ደጋፊዎች በተመሳሳይ 25 በመቶ ድምጽ አላቸው። ከእነዚህ ውስጥ የዓመቱ ምርጥ አትሌት የሚሆኑ አንድ ወንድና አንድ ሴት አትሌቶች በታህሳስ ወር መጀመሪያ በፈረንሳይ ሞናኮ ይፋ ይደረጋል። የድምጽ አሰጣጡ የሚቆየው እስከ ህዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም ነው።